Thursday, February 18, 2010

መጽሐፈ ነህምያ 1

ምዕራፍ 1።

1፤ የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል። በሀያኛው ዓመት በካሴሉ ወር እንዲህ ሆነ፤

2፤ እኔ በሱሳ ግንብ ሳለሁ፥ ከወንድሞቼ አንዱ አናኒ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሰዎች ከይሁዳ መጡ፤ እኔም የዳኑትን ከምርኮ የተረፉትን የአይሁድን ነገር የኢየሩሳሌምንም ነገር ጠየቅኋቸው።

3፤ እነርሱም። በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል አሉኝ።

4፤ ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፥ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፥

5፤ እንዲህም አልሁ። አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥

6፤ እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮህ ያድምጥ፥ ዓይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኃጢአት እናዘዝልሃለሁ፤ እኔና የአባቴም ቤት በድለናል።

7፤ እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዓት ሕግም አልጠበቅንም።

8፤9፤ አሁንም ብትተላለፉ በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፤ ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ ብታደርጓትም፥ ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ምንም ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፥ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ ብለህ ለባሪያህ ለሙሴ ያዘዝኸውን ቃል እባክህ አስብ።

10፤ እነዚህም በታላቅ ኃይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዠሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው።

11፤ ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን፥ የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፥ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው። እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊው ነበርሁ።

መጽሐፈ ነህምያ 2

ምዕራፍ 2።

1፤ በንጉሡ በአርጤክስስ በሀያኛው ዓመት በኒሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ በነበረ ጊዜ ጠጁን አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። ቀድሞ ግን በፊቱ ያለ ኃዘን እኖር ነበር።

2፤ ንጉሡም። ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኅዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ።

3፤ ንጉሡንም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ፤ የአባቶቼ መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አይዘን? አልሁት።

4፤ ንጉሡም። ምን ትለምነኛለህ? አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ።

5፤ ንጉሡንም። ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶቼ መቃብር ከተማ ስደደኝ አልሁት።

6፤ ንግሥቲቱም በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ። መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ? አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ዘመኑን ቀጠርሁለት።

7፤ ንጉሡንም። ንጉሡ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ አገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይሰጠኝ፤

8፤ በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ አልሁት። ንጉሡም በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነችው እንደ አምላኬ እጅ ሰጠኝ።

9፤ በወንዙም ማዶ ወዳሉት አለቆች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤ ሰጠኋቸው ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ሰደደ።

10፤ ሖሮናዊውም ሰንባላጥና ባሪያው አሞናዊ ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ።

11፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፥ በዚያም ሦስት ቀን ያህል ተቀመጥሁ።

12፤ በሌሊትም ተነሣሁ፥ ከእኔም ጋር አያሌ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም።

13፤ በሸለቆውም በር ወጣሁ፥ ወደ ዘንዶውም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ።

14፤ ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡ መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበትም የነበረው እንስሳ የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም።

15፤ በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ ዘወርም ብዬ በሸለቆው በር ገባሁ፥ እንዲሁም ተመለስሁ።

16፤ ሹማምቱ ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹማምቱም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች ገና አልተናገርሁም ነበር።

17፤ እኔም። እኛ ያለንበትን ጕስቍልና ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ፤ አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ አልኋቸው።

18፤ የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። እነርሱም። እንነሣና እንሥራ አሉ። እጃቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ።

19፤ ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ ባሪያውም አሞናዊው ጦብያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፥ ቀላል አድርገውንም። ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድር ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን? አሉ።

20፤ እኔም መልሼ። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም አልኋቸው።

መጽሐፈ ነህምያ 3

ምዕራፍ 3።

1፤ ታላቁም ካህን ኤልያሴብ ወንድሞቹም ካህናት ተነሥተው የበግ በር ሠሩ፤ ቀደሱትም፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፤ እስከ ሃሜአ ግንብና እስከ ሐናንኤል ግንብ ድረስ ቀደሱት።

2፤ በአጠገቡ የኢያሪኮ ሰዎች ሠሩ፤ በአጠገባቸውም የአምሪ ልጅ ዘኩር ሠራ።

3፤ የሃስናአ ልጆችም የዓሣ በር ሠሩ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።

4፤ በአጠገባቸውም የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት አደሰ። በአጠገባቸውም የሜሴዜቤል ልጅ የበራክያ ልጅ ሜሱላም አደሰ። በአጠገባቸውም የበዓና ልጅ ሳዶቅ አደሰ።

5፤ በአጠገባቸውም ቴቁሐውያን አደሱ፤ ታላላቆቻቸው ግን ለጌታቸው ሥራ አንገታቸውን አላዋረዱም።

6፤ የፋሴሐ ልጅ ዮዳሄና የበሶድያ ልጅ ሜሱላም አሮጌውን በር አደሱ፤ ሰረገሎቹን አኖሩ፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ።

7፤ በአጠገባቸውም ገባዖናዊው መልጥያና ሜሮኖታዊው ያዶን፥ የወንዙም ማዶ አለቃ ግዛት የሆኑ የገባዖንና የምጽጳ ሰዎች አደሱ።

8፤ በአጠገባቸውም ወርቅ አንጥረኛው የሐርሃያ ልጅ ዑዝኤል አደሰ። በአጠገቡም ከሽቱ ቀማሚዎች የነበረ ሐናንያ አደሰ፤ እስከ ሰፊው ቅጥር ድረስ ኢየሩሳሌምን ጠገኑ።

9፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታ አለቃ የሆር ልጅ ረፋያ አደሰ።

10፤ በአጠገባቸውም የኤርማፍ ልጅ ይዳያ በቤቱ አንጻር ያለውን አደሰ። በአጠገቡም የአሰበንያ ልጅ ሐጡስ አደሰ።

11፤ የካሪም ልጅ መልክያ፥ የፈሐት ሞዓብ ልጅም አሱብ ሌላውን ክፍልና የእቶኑን ግንብ አደሱ።

12፤ በአጠገባቸውም የኢየሩሳሌም ግዛት እኵሌታና የመንደሮችዋ አለቃ የአሎኤስ ልጅ ሰሎም አደሰ።

13፤ ሐኖንና የዛኖዋ ሰዎችም የሸለቆውን በር አደሱ፤ ሠሩት፥ ሳንቃዎቹንም አቆሙ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረጉ፤ ደግሞም እስከ ጕድፍ መጣያው በር ድረስ አንድ ሺህ ክንድ የሚሆን ቅጥር ሠሩ።

14፤ የቤትሐካሪምም ግዛት አለቃ የሬካብ ልጅ መልክያ የጕድፍ መጣያውን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ።

15፤ የምጽጳም ግዛት አለቃ የኮልሖዜ ልጅ ሰሎም የምንጩን በር አደሰ፤ ሠራው፥ ከደነውም፥ ሳንቃዎቹንም አቆመ፥ ቍልፎቹንና መወርወሪያዎቹንም አደረገ፤ ከዳዊትም ከተማ እስከሚወርደው ደረጃ ድረስ በንጉሡ አትክልት አጠገብ ያለውን የሼላን መዋኛ ቅጥር ሠራ።

16፤ ከእርሱም በኋላ የቤትጹር ግዛት እኵሌታ አለቃ የዓዝቡቅ ልጅ ነህምያ በዳዊት መቃብር አንጻር እስካለው ስፍራ፥ እስከ ተሠራውም መዋኛ፥ እስከ ኃያላኑም ቤት ድረስ አደሰ።

17፤ ከእርሱም በኋላ ሌዋውያንና የባኒ ልጅ ሬሁም አደሱ። በአጠገባቸውም የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ ሐሸብያ ስለ ግዛቱ አደሰ።

18፤ ከእርሱም በኋላ የቅዒላ ግዛት እኵሌታ አለቃ የኤንሐዳድ ልጅ በዋይ ወንድሞቹም አደሱ።

19፤ በአጠገቡም የምጽጳ አለቃ የኢያሱ ልጅ ኤጽር በማዕዘኑ አጠገብ በጦር መሣሪያ ቤት አንጻር ሌላውን ክፍል አደሰ።

20፤ ከእርሱም በኋላ የዘባይ ልጅ ባሮክ ከማዕዘኑ ጀምሮ እስከ ታላቁ ካህን እስከ ኤልያሴብ ቤት መግቢያ ድረስ ሌላውን ክፍል ተግቶ አደሰ።

21፤ ከእርሱም በኋላ የአቆስ ልጅ የኦርዮ ልጅ ሜሪሞት ከኤልያሴብ ቤት መግቢያ ጀምሮ እስከ ኤልያሴብ ቤት መጨረሻ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።

22፤ ከእርሱም በኋላ የቈላው ሰዎች ካህናቱ አደሱ።

23፤ ከእነርሱም በኋላ ብንያምና አሱብ በቤታቸው አንጻር ያለውን አደሱ። ከእነርሱም በኋላ የሐናንያ ልጅ የመዕሤያ ልጅ ዓዛርያስ በቤቱ አጠገብ ያለውን አደሰ።

24፤ ከእርሱም በኋላ የኤንሐደድ ልጅ ቢንዊ ከዓዛርያስ ቤት ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ ድረስ ሌላውን ክፍል አደሰ።

25፤ የኡዛይ ልጅ ፋላል በማዕዘኑ አንጻር ያለውንና በዘበኞች አደባባይ አጠገብ ከላይኛው የንጉሡ ቤት ወጥቶ የቆመውን ግንብ ሠራ። ከእርሱም በኋላ የፋሮስ ልጅ ፈዳያ ሠራ።

26፤ ናታኒምም በዖፌል በውኃው በር አንጻር በምሥራቅ በኩል ወጥቶ በቆመው ግንብ አጠገብ እስካለው ስፍራ ድረስ ተቀመጡ።

27፤ ከእርሱም በኋላ ቴቁሐውያን ወጥቶ በቆመው በታላቁ ግንብ አንጻር ያለውን እስከ ዖፌል ቅጥር ድረስ ሌላውን ክፍል አደሱ።

28፤ ከፈረሱ በር በላይ ካህናቱ እያንዳንዳቸው በየቤታቸው አንጻር አደሱ።

29፤ ከዚያ በኋላ የኢሜር ልጅ ሳዶቅ በቤቱ አንጻር አደሰ። ከእርሱም በኋላ የምሥራቁን በር ጠባቂ የሴኬንያ ልጅ ሸማያ አደሰ።

30፤ ከእርሱ በኋላ የሰሌምያ ልጅ ሐናንያና የሴሌፍ ስድስተኛው ልጁ ሐኖን ሌላውን ክፍል አደሱ። ከዚያም በኋላ የበራክያ ልጅ ሜሱላም በጓዳው አንጻር ያለውን አደሰ።

31፤ ከእርሱም በኋላ ከወርቅ አንጥረኞቹ የነበረ መልክያ እስከ ናታኒምና እስከ ነጋዴዎቹ ቤት ድረስ በሐሚፍቃድ በር አንጻር ያለውን እስከ ማዕዘኑ መውጫ ድረስ አደሰ።

32፤ ከማዕዘኑም መውጫ ጀምረው እስከ በጉ በር ድረስ ወርቅ አንጥረኞችና ነጋዴዎች አደሱ።

መጽሐፈ ነህምያ 4

ምዕራፍ 4።

1፤ ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ።

2፤ በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት። እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ።

3፤ አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ።

4፤ አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው።

5፤ በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና።

6፤ ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።

7፤ ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።

8፤ መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ።

9፤ ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን።

10፤ ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ።

11፤ ጠላቶቻችንም። ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ።

12፤ በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው። ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን።

13፤ ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው።

14፤ አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ። አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።

15፤ ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን።

16፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።

17፤ ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር።

18፤ አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ።

19፤ ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ። ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤

20፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።

21፤ ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኵሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር።

22፤ ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን። ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው።

23፤ እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።

መጽሐፈ ነህምያ 5

ምዕራፍ 5።

1፤ በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ።

2፤ አያሌዎቹም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው፤ በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር።

3፤ አያሌዎቹም። ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር።

4፤ ሌሎቹም። ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል፤

5፤ አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው፤ እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ፤ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር።

6፤ እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ።

7፤ በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም። ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው፤ ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው።

8፤ እኔም። ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን፤ እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም።

9፤ ደግሞም አልሁ። የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም፤ ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን?

10፤ እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል፤ እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው።

11፤ እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው።

12፤ እነርሱም። እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም፤ እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው።

13፤ ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና። ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው፤ እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ። አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ።

14፤ ንጉሡም በይሁዳ ምድር ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ካዘዘኝ ጊዜ ጀምሮ ከንጉሡ ከአርጤክስስ ከሀያኛው ዓመት እስከ ሠላሳ ሁለተኛው ዓመት ድረስ አሥራ ሁለት ዓመት ያህል እኔና ወንድሞቼ ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልበላንም።

15፤ ከእኔ አስቀድመው የነበሩት አለቆች ግን በሕዝቡ ላይ አክብደው ነበር፤ ስለ እንጀራውና ስለ ወይኑ አርባ ሰቅል ብር ይወስዱ ነበር፤ ሎሌዎቻቸውም ደግሞ በሕዝቡ ላይ ይሠለጥኑ ነበር፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈራሁ እንዲህ አላደረግሁም።

16፤ ደግሞም አጥብቄ የቅጥሩን ሥራ ሠራሁ፥ እርሻም አልገዛንም፤ ብላቴኖቼም ሁሉ ወደዚያው ወደ ሥራው ተሰበሰቡ።

17፤ ደግሞም በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ ወደ እኛ ከመጡት ሌላ ከአይሁድና ከሹማምቱ መቶ አምሳ ሰዎች በገበታዬ ነበሩ።

18፤ ከወፎችም በቀር ለአንድ ቀን አንድ በሬና ስድስት የሰቡ በጎች፥ በአሥር በአሥር ቀንም ብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት ወይን ጠጅ ይዘጋጅልኝ ነበር፤ ነገር ግን አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ከብዶ ነበርና ለአለቃ የሚገባውን ስንቅ አልሻም ነበር።

19፤ አምላኬ ሆይ፥ ለዚህ ሕዝብ ያደረግሁትን ሁሉ ለበጎነት አስብልኝ።

መጽሐፈ ነህምያ 6

ምዕራፍ 6።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንባላጥና ጦብያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር።

2፤ ሰንባላጥና ጌሳም። መጥተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ ብለው ላኩብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ያስቡ ነበር።

3፤ እኔም። ትልቅ ሥራ እሠራለሁ፥ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም፤ ሥራውን ትቼ ወደ እናንተ በመውረዴ ስለ ምን ሥራው ይታጐላል? ብዬ መልእክተኞችን ላክሁባቸው።

4፤ እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው።

5፤ ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ጊዜ ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤

6፤ በእጁም ውስጥ። አንተና አይሁድ ዓመፅ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል።

7፤ ደግሞም። ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፤ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፤ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር የሚል ክፍት ደብዳቤ ነበረ።

8፤ እኔም። አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት።

9፤ እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም። እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ፤ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ።

10፤ እኔም ወደ መሔጣብኤል ልጅ ወደ ድላያ ልጅ ወደ ሸማያ ቤት ገባሁ፤ እርሱም ተዘግቶ ነበርና። በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ ውስጥ እንገናኝ የመቅደሱንም ደጆች እንዝጋ፤ እነርሱ መጥተው ይገድሉሃልና፥ በሌሊትም ይገድሉህ ዘንድ ይመጣሉና አለ።

11፤ እኔም። እንደ እኔ ያለ ሰው የሸሸና፥ ነፍሱንስ ያድን ዘንድ ወደ መቅደስ የገባ ማን ነው? እኔስ አልገባም አልሁት።

12፤ እግዚአብሔርም ልኮት እንዳልነበረ፥ በእኔ ላይ ግን ትንቢት እንደ ተናገረ፥ እነሆ፥ አወቅሁ፤ ጦብያና ሰንባላጥም ገዝተውት ነበር።

13፤ ይህንም ነገር አደርግና እበድል ዘንድ፥ በእኔም ላይ ክፋት እንዲናገሩና እንዲያላግጡ ያስፈራራኝ ዘንድ ተገዝቶ ነበር።

14፤ አምላኬ ሆይ፥ ስለዚህ ሥራቸው ጦብያንና ሰንባላጥን ያስፈራሩኝም ዘንድ የወደዱትን ነቢይቱን ኖዓድያን የቀሩትንም ነቢያት አስብ።

15፤ ቅጥሩም በኤሉል ወር በሀያ አምስተኛው ቀን በአምሳ ሁለት ቀን ውስጥ ተጨረሰ።

16፤ ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፥ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፥ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ።

17፤18፤ ጦብያም የኤራ ልጅ የሴኬንያ አማች ስለ ነበረ፥ ልጁም ይሆሐናን የቤራክያን ልጅ የሜሱላምን ሴት ልጅ ስላገባ፥ በይሁዳ ብዙ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበርና በዚያ ወራት ብዙ የይሁዳ አለቆች ወደ ጦብያ ደብዳቤዎች ይልኩ ነበር፥ የጦብያም ደብዳቤዎች ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር።

19፤ ደግሞም በፊቴ ስለ እርሱ መልካም ይናገሩ ነበር፥ ቃሌንም ያወሩለት ነበር፤ ጦብያም ሊያስፈራራኝ ደብዳቤዎችን ይልክ ነበር።

መጽሐፈ ነህምያ 7

ምዕራፍ 7።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩ ከተሠራ በኋላ፥ ሳንቃዎቹንም ካቆምሁ በኋላ፥ በረኞቹና መዘምራኑ ሌዋውያኑም ከተሾሙ በኋላ፥

2፤ ወንድሜን አናኒንና የግንቡን አለቃ ሐናንያን በኢየሩሳሌም ላይ ሾምኋቸው፤ እርሱም እውነተኛ ከሌሎቹም ይልቅ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነበረ።

3፤ እኔም። ፀሐይ እስኪሞቅ ድረስ የኢየሩሳሌም በሮች አይከፈቱ፤ እነርሱም ቆመው ሳሉ ደጆቹን ይዝጉ፥ ይቈልፉም፤ ከኢየሩሳሌምም ሰዎች አንዳንዱን በየተራው አንዳንዱንም በየቤቱ አንጻር ጠባቆችን አስቀምጡ አልኋቸው።

4፤ ከተማይቱም ሰፊና ታላቅ ነበረች፤ በውስጥዋ የነበሩ ሕዝብ ግን ጥቂቶች ነበሩ፥ ቤቶቹም አልተሠሩም ነበር።

5፤ አምላኬም ታላቆቹንና ሹማምቱን ሕዝቡንም ሰብስቤ እቈጥራቸው ዘንድ በልቤ አደረገ፤ አስቀድመው የመጡትን ሰዎች የትውልድ መጽሐፋቸውን አገኘሁ፥ በእርሱም እንደዚህ ተጽፎ አገኘሁ።

6፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ ወደ እየከተማቸው የተመለሱት የአገር ልጆች እነዚህ ናቸው።

7፤ ከዘሩባቤል፥ ከኢያሱ፥ ከነህምያ፥ ከአዛርያስ፥ ከረዓምያ፥ ከነሐማኒ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከበላሳን፥ ከሚስጴሬት፥ ከበጉዋይ፥ ከነሑም፥ ከበዓና ጋር መጡ።

8፤ የእስራኤልም ሕዝብ ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤ የፋሮስ ልጆች፥ ሁለት ሺህ መቶ ሰባ ሁለት።

9፤ የሰፋጥያስ ልጆች ሦስት መቶ ሰባ ሁለት።

10፤ የኤራ ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ ሁለት።

11፤ ከኢያሱና ከኢዮአብ ልጆች የሆኑ የፈሐት ሞዓብ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ አሥራ ስምንት።

12፤ የኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት።

13፤ የዛቱዕ ልጆች፥ ስምንት መቶ አርባ አምስት።

14፤ የዘካይ ልጆች፥ ሰባት መቶ ስድሳ።

15፤ የቢንዊ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ስምንት።

16፤ የቤባይ ልጆች፥ ስድስት መቶ ሀያ ስምንት።

17፤ የዓዝጋድ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሀያ ሁለት።

18፤ የአዶኒቃም ልጆች፥ ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት።

19፤ የበጉዋይ ልጆች፥ ሁለት ሺህ ስድሳ ሰባት።

20፤ የዓዲን ልጆች፥ ስድስት መቶ አምሳ አምስት።

21፤ የሕዝቅያስ ወገን የአጤር ልጆች፥ ዘጠና ስምንት።

22፤ የሐሱም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ ስምንት።

23፤ የቤሳይ ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ አራት።

24፤ የሐሪፍ ልጆች፥ መቶ አሥራ ሁለት።

25፤ የገባዖን ልጆች፥ ዘጠና አምስት።

26፤ የቤተ ልሔምና የነጦፋ ሰዎች፥ መቶ ሰማንያ ስምንት።

27፤ የዓናቶች ሰዎች፥ መቶ ሀያ ስምንት።

28፤ የቤትዓዝሞት ሰዎች፥ አርባ ሁለት።

29፤ የቂርያትይዓሪምና የከፊራ የብኤሮትም ሰዎች፥ ሰባት መቶ አርባ ሦስት።

30፤ የራማና የጌባ ሰዎች፥ ስድስት መቶ ሀያ አንድ።

31፤ የማክማስ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሁለት።

32፤ የቤቴልና የጋይ ሰዎች፥ መቶ ሀያ ሦስት።

33፤ የሁለተኛው ናባው ሰዎች፥ አምሳ ሁለት።

34፤ የሁለተኛው ኤላም ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አምሳ አራት።

35፤ የካሪም ልጆች፥ ሦስት መቶ ሀያ።

36፤ የኢያሪኮ ልጆች፥ ሦስት መቶ አርባ አምስት

37፤ የሎድና የሐዲድ የኦኖም ልጆች፥ ሰባት መቶ ሀያ አንድ።

38፤ የሴናዓ ልጆች፥ ሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሠላሳ።

39፤ ካህናቱ፤ ከኢያሱ ወገን የዮዳኤ ልጆች፥ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሦስት።

40፤ የኢሜር ልጆች፥ ሺህ አምሳ ሁለት።

41፤ የፋስኮር ልጆች፥ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት።

42፤ የካሪም ልጆች፥ ሺህ አሥራ ሰባት።

43፤ ሌዋውያኑ፤ ከሆዳይዋ ወገን የኢያሱና የቀድምኤል ልጆች፥ ሰባ አራት።

44፤ መዘምራኑ፤ የአሳፍ ልጆች፥ መቶ አርባ ስምንት።

45፤ በረኞቹ፤ የሰሎም ልጆች፥ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሶባይ ልጆች፥ መቶ ሠላሳ ስምንት።

46፤ ናታኒም፥ የሲሐ ልጆች፥ የሐሡፋ ልጆች፥

47፤ የጠብዖት ልጆች፥ የኬራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፥

48፤ የፋዶን ልጆች፥ የልባና ልጆች፥

49፤ የአጋባ ልጆች፥ የሰምላይ ልጆች፥ የሐናን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥ የጋሐር ልጆች፥

50፤ የራያ ልጆች፥ የረአሶን ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥

51፤ የጋሴም ልጆች፥ የዖዛ ልጆች፥ የፋሴሐ ልጆች፥

52፤ የቤሳይ ልጆች፥ የምዑናውያን ልጆች፥

53፤ የንፉሰሲም ልጆች፥ የበቅቡቅ ልጆች፥ የሐቀፋ ልጆች፥ የሐርሑር ልጆች፥

54፤ የበስሎት ልጆች፥ የምሒዳ ልጆች፥ የሐርሻ ልጆች፥

55፤ የበርቆስ ልጆች፥ የሲሣራ ልጆች፥

56፤ የቴማ ልጆች፥ የንስያ ልጆች፥ የሐጢፋ ልጆች።

57፤ የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች፤ የሶጣይ ልጆች፥ የሶፌሬት ልጆች፥ የፍሩዳ ልጆች፥

58፤ የየዕላ ልጆች፥ የደርቆን ልጆች፥ የጌዴል ልጆች፥

59፤ የሰፋጥያስ ልጆች፥ የሐጢል ልጆች፥ የፈከራት ልጆች፥ የሐፂቦይም ልጆች፥ የአሞን ልጆች።

60፤ ናታኒም ሁሉና የሰሎሞን ባሪያዎች ልጆች ሦስት መቶ ዘጠና ሁለት ነበሩ።

61፤ ከቴልሜላ፥ ከቴላሬሳ፥ ከክሩብ፥ ከአዳን፥ ከኢሜር የወጡ እነዚህ ናቸው፤ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ቤቶችና ዘራቸውን ወይም ከእስራኤል ወገን መሆናቸውን ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም፤

62፤ የዳላያ ልጆች፥ የጦብያ ልጆች፥ የኔቆዳ ልጆች፥ ስድስት መቶ አርባ ሁለት።

63፤ ከካህናቱም የኤብያ ልጆች፥ የአቆስ ልጆች፥ ከገለዓዳዊው ከቤርዜሊ ልጆች ሚስት ያገባ በስሙም የተጠራ የቤርዜሊ ልጆች።

64፤ እነዚህ በትውልድ መጽሐፍ ትውልዳቸውን ፈለጉ፥ ነገር ግን አልተገኘም፤ ከክህነትም ተከለከሉ።

65፤ ሐቴርሰታም። በኡሪምና በቱሚም የሚፈርድ ካህን እስኪነሣ ደረስ ከተቀደሰው ነገር አትበሉም አላቸው።

66፤67፤ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ከነበሩ ከሎሌዎቻቸውና ከገረዶቻቸው ሌላ ጉባኤው ሁሉ አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ፤ ሁለቱ መቶም አርባ አምስት ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩአቸው።

68፤ ፈረሶቻቸውም ሰባት መቶ ሠላሳ ስድስት፥ በቅሎቻቸውም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥

69፤ ግመሎቻቸውም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥ አህዮቻቸውም ስድስት ሺህ ሰባት መቶ ሀያ ነበሩ።

70፤ ከአባቶች ቤቶች አለቆችም አያሌዎቹ ሰዎች ስለ ሥራው ስጦታ ሰጡ። ሐቴርሰታም አንድ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ አምሳም ድስቶች፥ አምስት መቶ ሠላሳም የካህናት ልብስ በቤተ መዛግብት ውስጥ ሰጠ።

71፤ ከአባቶች ቤቶች አለቆችም አያሌዎቹ በሥራው ቤተ መዛግብት ውስጥ ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክ፥ ሁለት ሺህ ሁለት መቶም ምናን ብር ሰጡ።

72፤ የቀሩትም ሕዝብ የሰጡት ሀያ ሺህ የወርቅ ዳሪክና ሁለት ሺህ ምናን ብር፥ ስድሳ ሰባትም የካህናት ልብስ ነበረ።

73፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም፥ በረኞቹና መዘምራኑም ከሕዝቡም አያሌዎቹ፥ ናታኒምም፥ እስራኤልም ሁሉ በከተሞቻቸው ተቀመጡ።